የተከበራችሁ የድረ-ገፃችን ተከታታዮቻችን፡፡ እንደምን ከረማችሁልን፡፡ ለዛሬ ይዘን የቀረብነዉ የሙስና ምንነት በሚል ርዕስ ሲሆን ስለርዕሰ ጉዳዩ መጠነኛ ግንዛቤ ታገኛላችሁ ብልን እናስባለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ሙስና እንደየ ሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ በተለያየ መንገድ መጠንና አይነት የሚከሰት በመሆኑ አንድ ወጥና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ትርጉም ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ እንደ ጉቦ የሚቆጠር ድርጊት በሌላው ማህበረሰብ እንደ ስጦታ ሊቆጠር ይችላል፡፡ እንዲሁም አንድ የፖለቲካ አመራር ወይም ኃላፊ ለቤተሰቡ ለጓደኞቹ ለፓርቲ ደጋፊዎች ከሥራው ጋር በተያያዘ ድጋፍ ቢያደርግ በአንዳንድ ማህበረሰብ ውስጥ እንደ ትክክለኛ ተግባር ሲወሰድ በሌላው ማህበረሰብ የሙስና ወንጀል ይሆናል(World Bank2006)፡፡ ከዚህ የተነሳ ብዙዎቻችን ስለ ሙስና ምንነት ግንዛቤ ቢኖረንም የሁላችንም ግንዛቤ ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል ማለት ነው፡፡
“Corruption” የሚለው ቃል”Corruptus” ከሚለው የላቲን ቃል የተወሰደ ሲሆን ሙስና ደግሞ “Corruption” የሚለውን የእንግሊዝኛውን ቃል እንዲገልጽ የምንጠቀምበት ከግዕዝ የተወረሰ ቃል ነው። ትርጉሙም ማጥፋት፣ ማበላሸት፣ ህግን መጣስ…. ወዘተ. ማለት ነው፡፡ በመስኩ ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ምሁራን፣ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ ድርጅቶች የተለያዩ መገለጫዎችን መሠረት በማድረግ ሙስና ለሚለው ቃል የሰጧቸው ትርጉሞች በአገላለጽ የተለያዩ ቢሆኑም በይዘታቸው ግን ተቀራራቢ ናቸው ፡፡ ለአብነት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ትርጉሞች እንመልከት፡-
ከላይ የቀረቡትን የሙስና ትርጉሞች ስናጤን ሙስና የሚለው ቃል በእርግጥም እጅግ በጣም ሰፊና ውስብስብ የሆኑ ኢ-ሥነምግባራዊ ተግባራትን እና የወንጀል ድርጊቶችን አካቶ መያዙን መረዳት ይቻላል። በተራ ቁጥር 1እና 2 የተገለጹትን ትረጉሞች ስንመለከት የሙስና ወንጀል በግልም ይሁን በመንግስት ተቋማት ውስጥ ሊፈጸም የሚችል መሆኑን የሚያሳዩ ሲሆን በሌላ በኩል ከ3-6 የተዘረዘሩት ሙስና በመንግስት ተቋማት የሚፈጸም ህገወጥ ድርጊት መሆኑን ያመለክታሉ::እነዚህ ድርጊቶች በግል ወይም በመንግስት ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ቢሆኑም አገሮች እንደሚያወጧቸው የፀረ-ሙስና ወንጀል ህጎች ትርጉሞቹ የተለያዩ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። በሀገራችን ሁኔታ በሀገር ሃብትና ሁለንተናዊ እድገት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የበለጠ ትኩረት የተሰጠው በመንግስትና በህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ በሚፈጸም ሙስና ላይ ነው፡፡ ከላይ ለሙስና የተሰጡት ትርጉሞች ስንመለከት በአጭሩ ሙስና ህግና ሥርአትን ተከትሎ ከመሰራት ይልቅ ስልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ ህግና ሥርአትን በመጣስ የመንግስትና የህዝብ ሃብትና ንብረትን በመስረቅ፣ በመዝረፍ፣ በማጭበርበር እንዲሁም በጉቦ፣ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በጎሰኝነት፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በኃይማኖት ትስስር ላይ በመመርኮዝ አድሏዊ በሆነ አሰራር ፍትህን እያዛቡ የግል ጥቅምን ማካበትና ሌላን ወገን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጥቀም ወይም ሙጉዳት እንደሆነ ከተሰጡት ትርጓሜዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡
ዉድ ተከታታዮቻችን በቀጣዩ ፅሁፋችን የሙስና ልዩ ባህሪያት ምን እንደሚመስሉ ይዘን እንቀርባለን፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡